በጉራፈርዳ የንጹሀን ዜጎች አሰቃቂ ግድያ

በጉራፈርዳ የንጹሀን ዜጎች አሰቃቂ ግድያ

   በደቡብ ክልል በጉራፈርዳ በንጹሀን ላይ የተፈጸመዉ ግድያዎች እጅግ አሳዝኖናል። የሀገራችን የሰላም ጉዳይ ከእለት ወደ እለት ይሻሻላል የሚል ተስፋ ብንሰንቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመምጣቱ ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ደረጃ በመድረሱ የሀገሪቱን ሰላም እየሽረሸረ ይገኛል።

   የንጹሀን ግድያና መፈናቀል በጣም ከመዘዉተሩ የተነሳ ሰምተንም ቢሆን  የማያስደነግጠንና የተለመደ እየሆነ የመምጣቱ ሂደቱ የምንጓዝበትን የለዉጥ መንገድ እንዳያሰናክልብንና የምናልማትን የበለጸገች ኢትዮጵያን የማየት ምኞታችንን እንዳያጨልምብን ቀድመን ነቅተን እንደ ዜጋም እንደ መንግስትም ልንከላከል የሚገባ ሲሆን በትክክል ችግራችንን ለይተን በጋራ በመቆም መፍትሄ ለመፈለግ ቁርጠኛ አቋም መዉሰድ ያለብን ወሳኝ ጊዜ ላይ ደርሰናል።

   የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ እና የማስጠበቅ ሀላፊነት ትልቁ ድርሻ የመንግስት በመሆኑ መንግስትም ይህንን ሀላፊነቱን በተገቢዉ መልኩ ሊወጣ ይገባል። ፍትህን ማስፈን ደግሞ ቅድሚያ የሚሰጠዉ ተግባር ከመሆኑ አንጻር መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታትና አገራዊ መግባባትን ለማስፈን በሁሉም መልኩ ጥረት ሊደረግ ይገባል።

    በጉራፈርዳ በደረሰዉ ጭፍጨፋ ህይወታቸዉን ያጡ ወገኖች እንደሰማነዉ አብዛኛዎቹ ሙስሊሞች መሆናቸዉና የተገደሉትም በመስጅድ በሰላም የአምልኮና የመማር ማስተማር ስራ ላይ ባሉበት ሁኔታና በተለይ ህጻናትን እና ነፍሰጡር እናቶችን ኢላማ ያደረገ መሆኑ ድርጊቱን የፈጸሙ አካላት ለሰዉ ልጆች ህይወትም ሆነ ለፈጣሪ ህግጋትም ደንታ ቢስነታቸዉ የደረሱበትን የጥላቻ ጥግ ያመላከታል።  

  በሀገሪቱ መሰል ችግሮች እንዳከሰቱ መከላከል እና ከተከሰቱም በኋላ ሳይድበሰበሱ በንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያን በሚፈጽሙ አካላት ላይ መንግስት ባለማመንታት ግልጽነት ባለዉ መልኩ አፋጣኝ ርምጃ በመዉሰድ ለህዝብ እንዲያሳዉቅ እንጠይቃለን።

 አላህ ሆይ ሀገራችንና ህዝባችንን ጠብቅልን ፤ አሜን

              በድር ኢትዮጵያ     ሰሜን አሜሪካ    ኦክቶበር 25 2020­­­

Leave a comment

All comments are moderated before being published